የ2018/19 የክረምት ወራት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ንቅናቄ “በጎነት ለኢትዮጵያ ከፍታ” በሚል መሪ ቃል፣ የኮንሶ ዞን ከፍተኛ አመራሮች፣ ወጣቶች እና የተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች በተገኙበት በካራት መጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል የሚገኙ ህሙማንን በመደገፍ በይፋ ተጀምሯል።

በማስጀመሪያ መርሃ ግብሩ ላይ የተናገሩ አመራሮች፣ በጎነት የህብረተሰብ አንድነትን፣ መተሳሰብንና አብሮነትን የሚያጠናክር ከፍተኛ ማህበራዊ እሴት መሆኑን ጠቅሰው፣ የዘንድሮው የክረምት ወራት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት እንቅስቃሴ የወጣቶችን ጉልበትና ዕውቀት በልማት ሥራዎች ላይ በማዋል የህዝቡን ችግሮች ለመቅረፍ ከፍተኛ ሚና እንደሚጫወት ገልጸዋል።
በዚህ ዓመት ከ95 ሺህ በላይ ወጣቶች በመሳተፍ ከ200 ሺህ በላይ የህብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ለማድረግ ታቅዶ የተጀመረ መሆኑ ተገልጿል። በተለያዩ የልማት፣ የአካባቢ ጥበቃ፣ የትምህርት፣ የጤና እና የማህበራዊ ድጋፍ መስኮች የሚከናወኑ ተግባራት የህዝብ ተሳትፎን በማጠናከር የኮንሶን የልማት ጉዞ የሚያፋጥኑ መሆናቸውም ተጠቁሟል።
በማስጀመሪያው መርሃ ግብር ላይ የኮንሶ ዞን ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኃላፊና የዞኑ ዋና የመንግስት ተጠሪ እንዲሁም የወጣቶች በጎ ፈቃድ አገልግሎት አብይ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ጉራሾ ለሚታ፣ የኮንሶ ዞን ወጣቶች ጉዳይና በጎ ፈቃድ አገልግሎት ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ከበደ ገለቱን ጨምሮ ሌሎች አመራሮች፣ ወጣቶች እና የማህበረሰብ ተወካዮች ተገኝተው መርሃ ግብሩን በይፋ አስጀምረዋል።
አመራሮቹ በመልዕክታቸው ወጣቶች በተለያዩ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት መስኮች በንቃት በመሳተፍ የመተጋገዝና የአብሮነት ባህልን እንዲያጎለብቱ ጥሪ ያቀረቡ ሲሆን፣ በዘንድሮው የክረምት ወራት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ንቅናቄ የታቀዱ ግቦች እንዲሳኩ ሁሉም አካላት በቅንጅት እንዲረባረቡ አሳስበዋል።
መረጃው፦ የኮንሶ ዞን መንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት
በጊያ ግና
ሰኔ 18/2018 ዓ.ም